ቤንያሚን ኔታንያሁ ጦራቸው በሄዝቦላህ ላይ "ጠንካራ እርምጃ" እንዲወስድ አዘዙ

የእስራኤል ጦር በደቡባዊ ሊባኖስ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, እስራኤል ደቡባዊ ሊባኖስን መቆጣጠሯን ቀጥለላች
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የተኩስ አቁም ስምምነቱ በሦስት ሳምንታት ከተራዘመ ከሁለት ቀናት በኋላ በሊባኖስ የሚገኙ የሄዝቦላህ ዒላማዎች ላይ "ከባድ ጥቃት" እንዲፈጽም ጦራቸውን አዘዙ።

አዲሱ የእስራኤል ጥቃቶች የተፈጸሙት መመሪያውን ተከትሎ ሲሆን፣ ቅዳሜ ዕለት በደቡባዊ ሊባኖስ በተፈጸሙ ድብደባዎች ቢያንስ ስድስት ሰዎች ከተገደሉ በኋላ ነው።

በሁለቱ ወገኖች መካከል የተደረጉ ተጨማሪ የድንበር ተሻጋሪ የተኩስ ልውውጦች ስምምነቱን ደካማ እና በቀላሉ ሊፈርስ የሚችል መሆኑን አሳይተዋል።

በሄዝቦላህ እና እስራኤል መካከል የሚደረገው ውጊያ ቀንሶ በነበረበት ወቅት ሐሙስ ዕለት በዋሽንግተን በተካሄደው የሁለቱ አገራት ልዑካን ውይይት የተኩስ አቁሙ ተራዝሟል።

ቅዳሜ ዕለት እስራኤል በናባቲህ በምትገኘው ዮህሞር አል-ሻኪፍ ከተማ በጭነት መኪና እና ሞተር ሳይክል ላይ በፈጸመችው ጥቃት አራት ሰዎችን መግደሏን የሊባኖስ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

በቢንት ጄቤይል በምትገኘው ሳፋድ አል ባቲች ከተማ ላይ በተፈጸመ ሌላ ጥቃት ሁለት ሰዎች መሞታቸውን እና 17 ሰዎች መቁሰላቸውን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

በሁለቱ አገራት መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት ቢደረስም እስራኤል አሁንም ደቡበዊ ሊባኖስ ውስጥ ወታደራዊ ዘመቻዎችን እያካሄደች ነው

የፎቶው ባለመብት, EPA

የእስራኤል የመከላከያ ሠራዊት ቅዳሜ ዕለት "በጦር መሳሪያ የጫነ ተሽከርካሪ" የሚያሽከረክሩ ሦስት የሄዝቦላህ አባላትን እንዲሁም ሌላ ሞተር ሳይክል የሚነዳን ግለሰብ "መግደሉን" አስታውቋል።

እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ ለምታካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ "በሠራዊቱ ላይ ስጋት ይደቅናሉ" በሚል የደህንነት ቀጣና በመሠረተችበት በሊታኒ አካባቢ ጦሩ ሁለት ተጨማሪ የታጣቂ ቡድኑ አባላት መገደላቸውን ገልጿል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የመከላከያ ሠራዊቱ በኋላ ላይ በማልኪያ አካባቢ "አጠራጣሪ የአየር ላይ ዒላማ መገኘቱን" በመግለጽ "ክስተቱ የተኩስ አቁም ስምምነቱን ተጨማሪ ጥሰት ነው" ብሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሄዝቦላህ ዮህሞር አል-ሻኪፍ ላይ ለተፈጸመው ጥቃት የአጸፋ እርምጃ በደቡባዊ ሊባኖስ የእስራኤልን የጦር ተሽከርካሪ ዒላማ እንዳደረገ አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።

ኔታንያሁ ቡድኑን ላይ ጠንካራ እርምጃ እንዲወሰድ ትዕዛዝ ከሰጡ በኋላ የሊባኖስ መንግሥት ብሔራዊ የዜና ኤጀንሲ (ኤንኤንኤ) በቢንት ጄቤይል በምትገኝ ከተማ፣ በታየር ባለች ከተማ እንዲሁም በናባቲህ ባሉ ሁለት ተጨማሪ ከተሞች ላይ ላይ ሁለት ተከታታይ ጥቃቶችን መፈጸማቸውን ዘግቧል።

የእስራኤል ጦር "በደቡባዊ ሊባኖስ ለወታደራዊ አገልግሎት የሚውሉ የሄዝቦላህ የሽብር መሠረተ ልማቶችን ተመትተዋል" ብሏል።

"ከፖለቲካ አመራሩ በተሰጠ መመሪያ መሠረት በእስራኤል ሲቪሎች እና በሠራዊቱ ወታደሮች ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን በመከላከል ቆራጥ እርምጃ እንደሚወስድ" ተናግሯል።

እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ የምታካሄደውን ወረራ የቀጠለች ሲሆን በርካታ መኖሪያ ቤቶችንም አፈራርሳለች።

አንድ ዓለም አቀፍ የፕሬስ ተሟጋች ቡድን ረቡዕ ዕለት በእስራኤል በተፈጸሙ ጥቃቶች አንድ ጋዜጠኛ መገደሏን ተከትሎ ቅዳሜ ዕለት ባወጣው መግለጫ በሊባኖስ በጋዜጠኞች ላይ የተሰነዘረው ጥቃት "ተቀባይነት የሌለው" መሆኑን ተናግሯል።

የሊባኖስ ባለሥልጣናት የጋዜጠኛዋን መገደል ተከትሎ ባወጡት መግለጫ የመጀመሪያው የአየር ጥቃት ከፊት ለፊታቸው የነበረውን ተሽከርካሪ በመምታቱ እና ሁለት ሰዎችን በመግደሉ ምክንያት በአንድ ቤት ውስጥ ተሸሽገው ባሉበት ሆን ተብሎ ዒላማ ተደርገዋል ሲል እስራኤልን ወንጅሏል።

የእስራኤል የመከላከያ ሠራዊት በበኩሉ ጋዜጠኞችን ዒላማ አላደረጉም ሲል አስተባብሏል።