ፓኪስታን ለሱዳን ልትሸጥ የነበረውን የጦር መሣሪያ በሳዑዲ አረቢያ ተቃውሞ ምክንያት ማዘግየቷን ሮይተርስ ዘገበ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ፓኪስታን ለሱዳን ልትሸጥ የነበረውን የጦር መሣሪያዎች እና ጄቶች ሽያጭ ሳዑዲ አረቢያ ስምምነቱ እንዲቋረጥ በመጠየቋ እና ግዢውን በገንዘብ እንደማትደግፍ በማሳወቋ የተነሳ ማዘግየቷን ምንጮች ለሮይተርስ ገለፁ።
ሁለት የፓኪስታን የደህንነት ምንጮች እና አንድ የዲፕሎማቲክ ምንጭ ለሮይተርስ እንደተናገሩት ፓኪስታን ለሱዳን ጦር ልትሸጣቸው የነበሩት የጦር መሣሪያዎች እና ወታደራዊ አውሮፕላኖች 1.5 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ነበሩ።
ከሦስት ዓመት በፊት በሱዳን ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች መካከል የተቀሰቀሰው የእርስ በእርስ ጦርነት በርካታ የሰብዓዊ ቀውሶችን አስከትሏል።
በጦርነቱ የተለያዩ የውጭ አገራት ሁለቱን ተፋላሚ ወገኖች በመደገፍ የሚሳተፉ ሲሆን ከፍተኛ የወርቅ አምራች የሆነችው አገር የመከፋፈል አደጋ ጋርጦባታል።
ሮይተርስ መጀመርያ ስለ ጦር መሣሪያው ግዢ ድርድር የዘገበው በጥር ወር ሲሆን በወቅቱ ሪያድ ስለምታደርገው የገንዘብ ድጋፍ በይፋ የሚታወቅ ነገር አልነበረም።
ይሁን እንጂ ሳዑዱ አረቢያ በሱዳን እና በፓኪስታን መካከል የሚደረገውን የመሳሪያ ግዢ ስምምነት በማደራደር ተሳትፋለች።
ፓኪስታን ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ ከሕንድ ጋር ፍጥጫ ውስጥ መግባቷን ተከትሎ የጄቶች እና የጦር መሳሪያዎቿ ዕውቅናን ካገኙ በኋላ የፓኪስታን ጦር ካደረጋቸው የተለያዩ የሽያጭ ስምምነቶች መካከል ይህ አንዱ ነው።
ሳዑዲ አረቢያ ከፓኪስታን የቅርብ አጋሮች መካከል አንዷ ስትሆን ለደከመው የኢዝላማባድ ኢኮኖሚ ወሳኝ የብድር እና የገንዘብ ምንጭ ሆና ቆይታለች።
በሁለቱም አገራት ላይ የሚሰነዘርን ጥቃት ለመከላከል የሚያስችል የጋራ መከላከያ ስምምነት ባለፈው ዓመት ከተፈራረሙ በኋላ ግንኙነታቸው እየጠነከረ መጥቷል።
አንድ የደህንነት ምንጭ "ሳዑዲ አረቢያ በገንዘብ የመደገፍ ሃሳቡን ከተወችው በኋላ ፓኪስታን ስምምነቱን እንድታቋርጥ አሳውቃታለች" ብለዋል።
የሳዑዲ መንግሥት የመገናኛ ብዙኃን ቢሮም ሆነ የሱዳን ጦር በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ አልሰጡም።
ሮይተርስ ለፓኪስታን ጦር ያቀረበው ጥያቄም ምላሽ አላገኘም።
የአገሪቱ ጦር እና አየር ኃይል አስቀድሞም ስምምነቱ እየተካሄደ ስለመሆኑ ማረጋገጫ አልሰጠም።
ምንጮች አንዳንድ የምዕራብ አገራት ሪያድ በአፍሪካ ከሚካሄደው የእጅ አዙር ጦርነት እጇን እንድትሰበስብ መክረዋታል ብለዋል።
ሳዑዲ አረቢያ እና ዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ ሱዳንን ጨምሮ በአፍሪካ የሚካሄዱ ግጭቶች ውስጥ ተፋላሚ ወገኖችን በመደገፍ ይታወቃሉ።
ሁለቱም ወገኖች ግጭቶች ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ እንዲያገኙ ጥረት እንደሚያደርጉ ቢናገሩም ሳዑዲ የሱዳን ጦርን ስትደግፍ ዩኤኢ ደግሞ ለአርኤስኤፍ ድጋፍ በማድረግ ስሟ ይነሳል።
ይህንን ግን የዩኤኢ መንግሥት ያስተባብላል።
አንድ የሮይተርስ ምንጭ የሱዳን ጦር አመራሮች እና የሳዑዲ ባለሥልጣናት በመጋቢት ወር በሪያድ ተገናኝተው ካደረጉት ውይይት በኋላ ሳዑዲ ስምምነቱን በፋይናንስ እንደማትደግፍ አሳውቃለች ብለዋል።
ሌላ ሁለተኛ የደህንንት ምንጭ ደግሞ ሳዑዲ አረቢያ ከሊቢያ ብሔራዊ ጦር ጋር ያደረገችው ሌላ የ4 ቢሊዮን ዶላር ስምምነትም አደጋ ላይ ወድቋል።
ለዚህም የተጠቀሰው ምክንያት ሳዑዲዎች በሁለቱም አገራት ላይ የሚከተሉትን "ስልት እንደገና እየተመለከቱት ነው" ብለዋል















