ሰሜን ኮሪያ በ13 ዓመት ውስጥ 358 ሰዎችን በሞት መቅጣቷን አንድ ሪፖርት አመለከተ

የሰሜን ኮሪያው ፕሬዚዳነት ኪም ጆንግ ኡን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሰሜን ኮሪያ እአአ ከ2011 እስከ 2024 ባሉት ዓመታት ውስጥ 358 ሰዎችን በሞት መቅጣቷን የአንድ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ሪፖርት አመለከተ
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በሰሜን ኮሪያ ከኮቪድ ወረርሽኝ በኋላ የሞት ቅጣት የሚፈጸምባቸው ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን መቀመጫውን ሴኡል ያደረገ አንድ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት አስታወቀ።

እንደ አውሮፓውያኑ ከጥር 2020 እስከ 2024 መጨረሻ ድረስ ቢያንስ 153 ሰዎቸ የሞት ቅጣት የተፈጸመባቸው ሲሆን፣ ይህም ከወረርሽኙ በፊት ከነበሩት አምስት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር በ44 ሰዎች ብልጫ አሳይቷል።

ትራንስናሽናል ጀስቲስ ወርኪንግ ግሩፕ የተባለው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ግለሰቦቹ የሞት ቅጣት የተፈጸመባቸው ከሃይማኖት፣ የውጭ አገር ፊልሞችን እና የቴሌቪዥን ድራማዎችን መመልከት እንዲሁም ከአጉል እምነቶች ጋር በተያያዘ ነው።

እአአ ከ2015 እስከ 2019 ባሉት ዓመታት ውስጥ የዓለም አቀፍ ጫና በመጠናከሩ ምክንያት የሞት ቅጣት የተፈጸመባቸው ሰዎች ቁጥር መቀነስ አሳይቷል።

ነገር ግን እአአ በ2020 እንደገና ፒዮንግያንግ ድንበሮቿን ከዘጋች በኋላ ቁጥሩ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን መንግሥታዊ ያልሆነው ድርጅት አስታውቋል።

ድርጅቱ በሰሜን ኮሪያ የሞት ቅጣት በኪም አገዛዝ የመጀመርያ ዓመታት ከፍ ብሎ ማግኘቱን ገልጿል።

እአአ በ2013 ብቻ 80 ሰዎች በሞት ተቀጥተዋል።

የመንግሥታቱ ድርጅት ፒዩንግያንግ ስልታዊ በሆነ መልኩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደምትፈጽም ከገለጸ በኋላ ቁጥሩ ቀንሷል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ነገር ግን እአአ በ2020 ቢያንስ 54 ሰዎች የሞት ቅጣት ሲፈጸምባቸው፣ በሚቀጥለው ዓመት ደግሞ 45 ሰዎች ተመሳሳይ ፍርድ ተፈጻሚ ሆኖባቸዋል።

ይህ እአአ ከ2016 እስከ 2019 ቢያንስ በዓመት አምሰት ሰዎች ላይ ብቻ የሞት ቅጣት ይፈጸም ከነበረባቸው ዓመታት ጋር ሲነጻጸር በጣም ከፍ ያለ ነው።

በኪም አስተዳደር ዘመን ከተፈጸሙ 144 የሞት ፍርዶች መካከል 29 የሚሆኑት ከሃይማኖት፣ ከአጉል እምነት እና የውጭ አገር ፊልሞችን ከመመልከት ጋር በተገናኘ የተገደሉ መሆናቸውን ድርጅቱ ጨምሮ ገልጿል።

የደበብ ኮሪያ ሙዚቃዎች እና ድራማዎች በሰሜን ኮሪያ ክልከላ ተጥሎባቸዋል። ተመራማሪዎች የኪም አገዛዝ የደቡብ ኮሪያ ድራማ እና ሙዚቃዎቹ መስፋፋትን ለርዕዮተ ዓለሙ ስጋት አድርጎ እንደሚመለከታቸው ይናገራሉ።

እአአ በ2024 ሁለት ታዳጊዎች የደቡብ ኮርያ ድራማዎችን በመመልከታቸው ብቻ ለ12 ዓመት በከባድ የጉልበት ስራ ላይ እንዲሰማሩ በአደባባይ ቅጣት ሲጣልባቸው የሚያሳይ ቪዲዮ ይፋ ሆኖ ነበር።

በሰሜን ኮሪያ የሞት ቅጣት የሚያስፈርጁ ሌሎች ጥፋቶች ኪምን ወይም ፓርቲያቸውን መተቸት፣ ሆን ተብሎ የሚፈጸም ግድያ፣ የአደንዛዥ ዕጽ ማዘዋወር እና ሰዎች ከአገሪቱ እንዲኮበልሉ እገዛ ማድረግ መሆናቸውን መቀመጫውን ደቡብ ኮሪያ ያደረገው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ገልጿል።

እአአ ከ2011 እስከ 2024 ድረስ ብቻ 358 ሰዎች በሞት ተቀጥተዋል ያለው ድርጅቱ፣ ከአገራቸው ከኮበለሉ 250 ሰሜን ኮሪያውያን ምስክርነቶችን መሰብሰቡን ጨምሮ ገልጿል።

70 በመቶ የሚሆኑት የሞት ቅጣቶች የተፈጸሙት በአደባባይ ሲሆን፣ አብዛኞቹ በጥይት ተመትተው እንዲሞቱ መደረጉ ተገልጿል።

የተባበሩት መንግሥታት የሰሜን ኮሪያ መንግሥት ዜጎቹ የውጭ አገር ፊልሞችን እና የቴሌቪዥን ድራማዎችን በማየታቸው የሞት ቅጣት እንደምትፈጽም በሪፖርቱ አመለከተ።

ከተቀረው ዓለም የተገለለችው እና በአምባገነን መንግሥት የምትተዳደረዋ ሰሜን ኮሪያ፣ የዜጎቿን ነጻነት ከመገደብ ባለፈ በግዳጅ ሥራ ላይ እንደሚያሰማሩ ሪፖርቱ ጠቅሷል።

የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ቢሮ ባለፉት አስር ዓመታት የሰሜን ኮሪያ መንግሥት "በዜጎቹ ሕይወት ላይ በሁሉም መስክ" የሚያደርገውን ቁጥጥር ማጥበቁን ገልጿል።