ቀጥታ, የሆርሙዝ እገዳ መጀመሩን ተከትሎ ፕሬዝዳንት ትራምፕ የኢራን መርከቦች ጥቃት እንደሚፈጸምባቸው አስጠነቀቁ

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሆርሙዝ ወሽመጥን ለመዝጋት ያስቀመጡት የጊዜ ገደብ መድረሱን ተከትሎ፤ የአሜሪካ ባሕር ኃይል ወደ ጣለውን እገዳ የሚጠጉ የኢራን “የጥቃት መርከቦች ይወገዳሉ” ሲሉ አስጠነቀቁ። ሦስት የአሜሪካ የጦር መርከቦች ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ ባልታየ ደረጃ ወደ ኦማን ባሕረ ሰላጤ ተጠግተዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. የፓኪስታኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ጦርነቱን ለማስቆም አሁንም ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናገሩ

    የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሼህባዝ ሻሪፍ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የቅዳሜ ዕለቱን ድርድር ያስተናገዱት የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሼህባዝ ሻሪፍ፤ በአሜሪካ እና ኢራን መካከል የሚደረገውን ጦርነት ለመቋጨት የሚደረገው ጥረት መቀጠሉን ተናገሩ።

    የሁለቱ አገራት ልዑኮች ከትናንት በስቲያ በፓኪስታን ዋና ከተማ ኢስላማባድ ተገኝተው ለ21 ሰዓታት የዘለቀ ድርድር ቢያደርጉም ስምምነት ላይ ሳይደርሱ ተለያይተዋል።

    የፓኪስታኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዛሬ ባስተላለፉት መልዕክት “ጉዳዩን ለመፍታት ሙሉ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ልነግራችሁ እፈልጋለሁ” ብለዋል።

    “የተኩስ አቁሙ አሁንም ዘልቋል፤ አሁን የተናገርኩ ባለሁበት ሰዓት ቀሪ ጉዳዮችን ለመፍታት ጥረቶች እየተደረጉ ነው” ሲሉ ለካቢኔያቸው መናገራቸውን የዜና ወኪሊ አጃንስ ፍራንስ ፕረስ (ኤኤፍፒ) ዘግቧል።

  2. ትራምፕ ወደ አሜሪካ እገዳ የሚጠጉ የኢራን መርከቦች ጥቃት እንደሚፈጸምባቸው አስጠነቀቁ

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሆርሙዝ ወሽመጥን ለመዝጋት ያስቀመጡት የጊዜ ገደብ መድረሱን ተከትሎ፤ የአሜሪካ ባሕር ኃይል ወደ ጣለውን እገዳ የሚጠጉ የኢራን “የጥቃት መርከቦች ይወገዳሉ” ሲሉ አስጠነቀቁ።

    ፕሬዝዳንቱ በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፤ እስካሁን ኢራን ላይ ጥቃት በሚፈጸምበት ወቅት “ፈጣን አጥቂ” ሲሉ የጠሯቸው የኢራን መርከቦች በአሜሪካ አለመመታታቸውን ገልጸዋል።

    “የኢራን ባሕር ኃይል የባሕሩ ወለል ላይ ተኝቷል፤ ሙሉ በሙሉ ተደምስሷል፤ 158 መርከቦች ወድመዋል” ሲሉ ጽፈዋል።

    “ያልመታናቸው ‘ፈጣን አጥቂ መርከቦች’ ብለው የሚጠሯቸውን ነው፤ ምክንያቱም እምብዛም ስጋት ናቸው ብለን አንቆጥራቸውም” ብለዋል።

    አክለውም፤ “ከእነዚህ መርከቦች የትኛውም ወደ ጣልነው እገዳ የሚመጣ ከሆነ፤ ባሕር ላይ በነበሩ የአደንዛዥ እፅ ሻጮች ጀልባዎች ላይ የተጠቀምነው የግድያ ስርዓት በመጠቀም ወዲያውኑ ይወገዳል” በማለት አስጠንቅቀዋል።

    የትራምፕ አስተዳደር ከመስከረም አንስቶ በካረቢያን ባሕር እና በፓስፊክ ውቅያኖስ ላይ በርካታ ገዳይ ጥቃቶችን ፈጽሟል። በእነዚህ ጥቃቶች አደንዛዥ እፅ አዘዋዋሪ ናቸው የተባሉ 130 ሰዎች ተገድለዋል።

  3. የአሜሪካ አውሮፕላን ተሸካሚን ጨምሮ ሦስት የጦር መርከቦች በኦማን ባሕረ ሰላጤ አቅራቢያ ታዩ

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ኢራን ወደቦች የሚጓዙ እና ከወደቦቹ የሚወጡ መርከቦችን እንቅስቃሴ ለማገድ ያስቀመጡት የጊዜ ገደብ 11 ሰዓት ላይ ተጀምሯል።

    ቢቢሲ ቬሪፋይ የሳተላይት ምስሎችን በመጠቀም የፕሬዝዳንቱ እገዳ ምን ሊመስል እንደሚችል ለመረዳት ሲሞክር ቆይቷል።

    ቅዳሜ ዕለት የተነሱ ሳተላይት ምስሎች እንደሚያሳዩት ግዙፉ የአሜሪካ አውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ ‘ዩኤስኤስ አብራሃም ሊንከን’ በኦማን ባሕረ ሰላጤ ምሥራቃዊ ጫፍ በኩል ይገኛል።

    ግዙፉ የጦር መርከብ ያለበት ርቀት ከኢራን የባሕር ዳርቻዎች ያለው ርቀት 200 ኪሎ ሜትር ገደማ ነው።

    የኢራን ጦርነት ከተጀመረ አንስቶ ይህ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ የታጠቀ መርከብ በዚህ ልክ ወደ ባሕረ ሰላጤው ቀርቦ ታይቶ አይታወቅም።

    በሳተላይት ምስሉ ላይ የሚታዩት በቅርብ ያሉ ሌሎች መርከቦች ያላቸው ቅርጽ እና ግዝፈት ከአሜሪካ ባሕር ኃይል የሚሳዔል አውዳሚ መርከቦች ጋር ተመሳሳይ ነው።

    እነዚህ መርከቦች ከአውሮፕላን ጫኙ ‘ዩኤስኤስ አብራሃም ሊንከን’ ጋር በአንድነት እንቅስቃሴ የሚያደርጉ እንደሆኑ ይገመታል። ይሁን እንጂ ምስሉ ላይ የሚታዩት የትኛዎቹ መርከቦች እንደሆኑ በትክክል መለየት አልተቻለም

    የጦር መርከቦቹን የሚያሳይ የሳተላይት ምስል
  4. ትንታኔ፡ አሜሪካን የበለጠ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ የሚከትተው የሆርሙዝ ወሽመጥ እገዳ

    በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የሚጓዙ መርከብ እና ፈጣን ጀልባ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    አሜሪካ ወደ ኢራን ወደቦች የሚደረግ ጉዞን የማገድ እርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀቷ በሕጋዊ፣ ወታደራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ከዚህ ቀደም ገብታበት የማታውቀው አደገኛ ቀጣና ውስጥ ያስገባታል ይላል የቢቢሲ የደኅንነት ጉዳዮች ዘጋቢው ፍራንክ ጋርድነር።

    እንደ ጋርድነር ትንተና፤ አሜሪካ እገዳውን ማስፈጸም ብትችልም የተወሰነ ስጋት ይጋረጥባታል።

    አሁን የአሜሪካ ባህር ኃይል ጦር መርከቦች እንቅስቃሴ እንደ ሴይ፣ ባንዳር አባስ እና ጃስክ ባሉ ወደቦች አቅራቢያ በማንዣበብ ብቻ አያበቃም። ይህ ደግሞ በድሮን፣ በሚሳዔል ወይም በአጥፍቶ ጠፊ ‘ካሚካዚ’ ፈጣን ጀልባዎች ለሚፈጸሙ ጥቃቶች እንዲጋለጡ ያደርጋል።

    የአሜሪካ ጦርን የመካከለኛው ምሥራቅ እንቅስቃሴን የሚሸፍነው ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም)፤ የትኛዎቹ መርከቦች የኢራን እንደሆኑ እና የትኛዎቹ ከኢራን ወደቦች እንደተነሱ ለማረጋገጥ የሳተላይት ምስል እና ሌሎች የስለላ መረጃዎችን ሊጠቀም ይችላል።

    መርከቦቹ፤ ጉዟቸውን ለመከታተል የሚያስችለውን የመለያ ስርዓት (AIS - automatic identification system) ቢያጠፉም እንኳ፤ ልክ የኦማን ባሕረ ሰላጤ ውስጥ እንደገቡ በአካባቢው በሚንቀሳቀሱት የአሜሪካ ጦር መርከቦች መገኘታቸው እና መያዛቸው አይቀርም።

    ኢራን ይህንን የአሜሪካ ዛቻ የባሕር ላይ ውንብድና ስትል ጠርታዋለች። ቴህራን የሆርሙዝ ወሽመጥን ስትዘጋ ተመሳሳይ አይነት ክስ ቀርቦባት ነበር።

    እስላማዊው ሪፐብሊክ በባሕረ ሰላጤው አገራት ወደቦች ላይ አጸፋ እርምጃ እንደሚወስድም አስጠንቅቋል።

    የኢራን አጋር የሆኑት ቻይና እና ሩሲያ ነገር ሌላኛው ጥያቄ የሚያስነሳ ጉዳይ ነው። በእርግጥ አሜሪካ ንብረትነቱ የቻይና የሆነ መርከብ ወይም ጭነት ላይ ወታደሮቿ እንዲወጡ ለማድረግ ወይም መርከቡን በቁጥጥር ስር ለማዋል ዝግጁ ነች?

    ብዙም ሳይርቅ ጅቡቲ ውስጥ ወታደራዊ ሠፈር ያላት ቻይና፤ መርከቦቿን በታጠቀ የባሕር ኃይሏ ለማጀብ ከወሰነችስ ምን ይፈጠራል?

  5. የአሜሪካ ጦር የሆርሙዝ እገዳን ጥሰው የሚጓዙ መርከቦች “እንደሚጠለፉ” አስጠነቀቀ

    በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚጓዝ መርከብ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የአሜሪካ ጦር፤ በኦማን ባሕረ ሰላጤ እና ከሆርሙዝ ወሽመጥ በስተምሥራቅ በሚገኘው የአረቢያን ባሕር ላይ የተጣለውን እገዳ ለማስፈጸም መዘጋጀቱን እንዲሁም እርምጃው መርከቦች ያነገቡትን ባንዲራ ሳይለይ በሁሉም ላይ ተፈጻሚ እንደሚሆን ማስታወቁ ተዘገበ።

    የአሜሪካ ጦር ማዕከላዊ ዕዝ ይህንን ያለው ከአንድ ሰዓት በኋላ ተግባራዊ እንደሚሆን የሚጠበቀው ዕገዳ ከመጀመሩ አስቀድሞ ለባሕርተኞች በላከው መልዕክት እንደሆነ የዜና ወኪሉ ሮይተርስ ገልጿል።

    ሮይተርስ የተመለከተው የዕዙ ማስታወሻ፤ “ፈቃድ ሳያገኝ ዕገዳ ወደተጣለበት አካባቢ የሚገባ ወይም ከዚያ የሚወጣ ማንኛውም መርከብ ለጠለፋ፣ አቅጣጫ ማስቀየር እና በቁጥጥር ስር መዋል እርምጃዎች ይዳረጋል” ይላል።

    "እገዳው በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ወደ ኢራን ወይም ከ[ኢራን] ወዳልሆኑ መዳረሻዎች የሚደረጉ ገለልተኛ የትራንዚት ጉዞዎችን አያስቆምም" ሲልም ያብራራል።

    የኮንትሮባንድ ጭነት መኖር እና አለመኖሩን ለማረጋገጥ ሲባል ገለልተኛ መርከቦች ፍተሻ ሊደረግባቸው እንደሚችል ለባሕርተኞች የተላከው ማስታወሻ ገልጿል።

    እንደ ምግብ፣ የህክምና አቅርቦቶች እና ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶች ያሉ ሰብአዊ ጭነቶች ፍተሻ ተደርጎባቸው ጉዞ እንዲያደርጉ እንደሚፈቀድላቸው መግለጹንም ዘገባው ያመለክታል።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከዛሬው ዕለት ጀምሮ ይተገበራል ያሉት እገዳ ተፈጻሚ መሆን የሚጀምረው 11 ሰዓት ላይ ነው።

    የአሜሪካ ጦር ማዕከላዊ ዕዝ በላከው ማስታወሻ፤ እገዳው የኢራንን ወደቦች እና የነዳጅ ማደያ ተርሚናሎችን ጨምሮ መላው "የኢራን የባህር ዳርቻን" እንደሚያካትት አስታውቋል። ሆኖም እርምጃው የኢራንን ወደቦች እና የነዳጅ ማደያ ተርሚናሎች ላይ “ብቻ እንደማይወሰን” ገልጿል።

  6. እስራኤል፤ አሜሪካ የሆርሙዝ ወሽመጥን መዝጋቷን እንደምትደግፍ አስታወቀች

    የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔትያናሁ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔትያናሁ አሜሪካ ወደ ኢራን ወደቦች የሚደረጉ የባሕር ጉዞዎችን ማገዷን እንደሚደግፉ ተናገሩ።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለካቢኔያቸው በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት፤ “ፕሬዝዳንት ትራምፕ የባሕር ጉዟቸው ላይ እገዳ ለመጣል ወስነዋል። በእርግጥም ይህንን ጠንካራ አቋም እንደግፋለን” ብለዋል።

    አሜሪካ እና ኢራን ፓኪስታን ውስጥ ካደረጉት ውጤት አልባው ንግግር በኋላ እሁድ ዕለት ከምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ ጋር መነጋገራቸውንም ገልጸዋል።

    ቫንስ “ዋነኛው ጉዳይ ሁሉንም የበለጸጉ [የኒውክሌር] ቁሶች ማስወገድ እና ምንም ተጨማሪ የማበልጸግ ተግባር እንደማይኖር ማረጋገጥ ላይ ያተኮረ ነበር” ሲሉ እንደነገሯቸው በኔትያናሁ በቪዲዮ መልዕክታቸው አንስተዋል።

    እንደ ኔትያናሁ ገለጻ የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ከፓኪስታ የተመለሱበት አውሮፕላን ውስጥ ሆነው የደወሉላቸው ሲሆን ከኢራን ጋር የሚደረገው ንግግር ደረሰበትን ደረጃ በተመለከተ ዝርዝር ማብራሪያ ሰጥተዋቸዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም፤ አሜሪካ እና እስራኤል ያላቸው ግንኙነት በመካከላቸው መራራቅ እንዳለ ከሚጠቁሙ አስተያየቶች “ፍጹም ተቃራኒ” እንደሆነ ተናግረዋል።

  7. ፈረንሳይ እና ዩናይትድ ኪንግደም የሆርሙዝ ወሽመጥን የተመለከተ ኮንፈረንስ ሊያዘጋጁ ነው

    የዩኬው ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር እና የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን፤ አገራቸው እና ዩናይትድ ኪንግደም “በመጪዎቹ ቀናት” በሆርሙዝ “ወሽመጥ ላይ የመርከብ ጉዞ ነጻነት መመለስን የተመለከተ” ኮንፈረንስ እንደሚያዘጋጁ አስታወቁ።

    ይህ እርምጃ “የመከላከል ተልዕኮ ብቻ” እንደሆነ በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ የገለጹት ማክሮን፤ “ከግጭቱ ተዋጊ ወገኖች የተነጠለ” እና “ሁኔታው እንደፈቀደ ተግባራዊ ሊደረግ የታቀደ” መሆኑንም አስረድተዋል።

    የዩኬው ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመርም በተመሳሳይ ሁለቱ አገራት በጋራ የሚያስተናግዱት ጉባኤ "ግጭቱ ሲያበቃ ዓለም አቀፍ የመርከብ ጉዞን ደኅንነት ለማስጠበቅ የተቀናጀ፣ ገለልተኛ፣ ዓለም አቀፍ እቅድ ለማዘጋጀት" ያለመ እንደሆነ ገልጸዋል።

    አሜሪካ በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ወደ ወይም ከኢራን ወደቦች የሚደረጉ ጉዞዎችን እንደምትዘጋ መግለጿን ተከትሎ በባሕረ ሰላጤው ውጥረቱ አይሏል።

    ዩናይትድ ኪንግደም አሜሪካ ልትወስድ ያቀደችውን እርምጃ እንደማትደግፍ አስታውቃለች። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስታርመር “የኢነርጂ ዋጋ በተቻለ ፍጥነት እንዲቀንስ የምናደርግበት መንገድ ይህ ነው” ሲሉ የሚደግፉት የሆርሙዝ ወሽመጥ መከፈትን እንደሆነ ገልጸዋል።

    ዩናይትድ ኪንግደም ከዚህ ቀደም በወሽመጡ ላይ የጉዞ ነጻነት እንዲረጋገጥ የማድረግ ግብ ያላቸው ከ40 በላይ አገራት ወኪሎችን ሰብስባ እንደነበር ይታወሳል።

  8. ፖፕ ሊዮ የትራምፕ አስተዳደርን “አልፈራም” ሲሉ ከፕሬዝዳንቱ ለቀረበባቸው ከባድ ትችት ምላሽ ሰጡ

    የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፤ የትራምፕ አስተዳደርን “እንደማይፈሩ” እንዲሁም የኢራን ጦርነትን በተመለከተ በያዙት አቋም ምክንያት ከፕሬዝዳንቱ ያልተለመደ ጥቃት ቢሰነዘርባቸውም ግጭቱን መቃወም እንደሚቀጥሉ ተናገሩ።

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው በለጠፉት ጽሑፍ፤ “ወንጀል ላይ ደካማ፣ ውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ የከፋ” ሲሉ ፖፕ ሊዮን ወቅሰዋል። ቆይተው ደግሞ “አድናቂው አይደለሁም” ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

    ወደ አልጄሪያ እየተጓዙ የነበሩት ፖፕ ሊዮ በበኩላቸው ከትራምፕ ጋር ክርክር ውስጥ መግባት እንደማይፈልጉ፤ ነገር ግን ስለ ሰላም መናገራቸውን እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

    ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የኢራን ጦርነት ላይ ብርቱ ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ቆይተዋል። ትራምፕ የኢራንን ሥልጣኔ እንደሚያወድሙ በተናገሩ ጊዜም ዛቻውን “ተቀባይነት የሌለው” በማለት ተችተዋል። ትራምፕ ጦርነቱን ለመቋጨት ሰላማዊ መንገድ እንዲፈልጉም መክረዋል።

    የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ከዓለም መሪዎች ለሚሰጡ አስተያየቶች ቀጥታ ምላሽ መስጠታቸው የተለመደ አይደለም።

    ፖፕ ሊዮ አካሄዳቸውን እንዲያስተካክሉ የሚገልጽ ጽሑፍ እሁድ ዕለት ማኀበራዊ ሚዲያ ላይ የለጠፉት ትራምፕ፤ “ኒውክሌር መሣሪያ ላይ ደካማ” ነበር ሲሉ አሜሪካ ከኢራን ጋር ጦርነት ያስገባትን ‘ቴህራን የኒውክሌር መሣሪያ ልትገነባ ነው’ የሚል ክስ ጠቅሰዋል።

    ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መሪ ሆነው የተመረጡት “አሜሪካዊ ስለሆነ ነው፤ ከፕሬዝዳንት ዶናልድ ጄ ትራምፕ ጋር በተያያዘ መፍትሔ ማግኛው ጥሩ መንገድ ይሄ ነው ብለው አስበው ነበር” ሲሉም ጽፈዋል።

    ወደ አልጄሪያ በሚጓዙበት አውሮፕላን ውስጥ ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ ለትራምፕ አስተያየት ምላሽ የሰጡት ፖፕ ሊዮ፤ ራሳቸውን ፖለቲካ ውስጥ ሚና እንዳለው ሰው እንደማይመለከቱ፤ ይልቁንም የሰላም መልዕክትን እንደሚያስተላልፉ ተናግረዋል።

    “የትራምፕ አስተዳደርን ወይም የወንጌል መልዕክትን ከፍ ባለ ድምጽ መናገርን አልፈራም፤ እዚህ ያለሁትም ይህንን ለማድረግ እንደሆነ ነው የማምነው፤ ቤተ ክርስቲያኗም ለዚሁ ነው ያለችው” ብለዋል።

    “ዛሬ በዓለም ላይ እጅግ በርካታ ሰዎች እየተሰቃዩ ነው። እጅግ ብዙ ንጹኃን ሰዎች እየተገደሉ ነው። የሆነ ሰው መነሳት እና ‘ይህንን ለማድረግ የተሻለ መንገድ አለ’ ብሎ መናገር አለበት” ሲሉ አቋማቸውን አሳውቀዋል።

  9. የአሜሪካ የባሕር ኃይል እርምጃ ቻይናን ለምን ሊጎዳ ይችላል?

    ቻይና በዓለም ላይ ድፍድፍ ዘይት ነዳጅን በብዛት ከሚገዙ አገራት መካከል ቀዳሚዋ ነች

    የፎቶው ባለመብት, NurPhoto via Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ቻይና በዓለም ላይ ድፍድፍ ዘይት ነዳጅን በብዛት ከሚገዙ አገራት መካከል ቀዳሚዋ ነች

    ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ባሕር ኃይል የኢራንን ወደቦችን መዝጋት እንደሚጀምሩ ሲዝቱ የቻይና መንግሥት ሁለቱም ወገኖች እንዲረጋጉ እና እንዲታቀቡ ጥሪ አቅርቧል።

    ቻይና በሳምንቱ መጨረሻ በፓኪስታን በተካሄደው የሰላም ድርድር ላይ ቴህራን እንድትገኝ ለማሳመን ተሳትፎዋ ምን አንደነበር እስካሁን በይፋ ያለችው ነገር የለም።

    ነገር ግን ቤይጂንግ ይህ ጦርነት እንዲቆም እንደምትፈልግ ምንም ጥርጥር የለውም።

    ቻይና በመካከለኛው ምሥራቅ የሚካሄደው ጦርነት እንዲቆም የምትፈልገው የኢራንን ነዳጅ ስለምትፈልግ ብቻ አይደለም።

    ኢራን ለቻይና የምታቀርበው የድፍድፍ ነዳጅ ዘይት የፍላጎቷን 13 በመቶ ብቻ ነው። አስፈላጊ ከሆነ ቤይጂንግ ይህንን ከሌላ ቦታ መሸመት ትችላለች።

    ነገር ግን የሆርሙዝ ወሽመጥ እንደ ሳዑዲ አረቢያ፣ ኢራን እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ካሉ ሌሎች የባህረ ሰላጤው አገራት ለምታገኘው የኢነርጂ አቅርቦቶች ቁልፍ የትራንስፖርት መስመር ነው።

    ቤይጂንግ ከዋሽንግተን ጋር የንግድ ጦርነት ውስጥ በገባችባቸው ባለፉት ዓመታት የመካከለኛው ምሥራቅ ለቻይና በጣም ወሳኝ ሆኗል። ቻይና ወደ መካከለኛው ምሥራቅ የምታደርገው የውጭ ንግድ በ2025 ወደ ሌላ ዓለም ከምትልከው በእጥፍ እድገት አሳይቷል።

    የቻይና እውነተኛ ፍላጎቶች ያለው እዚህ ላይ ነው። ኢኮኖሚዋ በዓለም ዙሪያ ላሉ አገሮች ምርቶቿን በመሸጥ ላይ በእጅጉ ያተኮረ ሲሆን፣ ዓለም አቀፍ አለመረጋጋት ለቤይጂንግ ከባድ ስጋት ይሆናል።

    ፕሬዝዳንት ዢ አሜሪካ እንዲህ ባለ ስትራቴጂካዊ የባሕር ትራንስፖርት መስመር ላይ የተቆጣጣሪነት ምንም አይነት ሚና እንዲኖራት አይፈልጉም።

    ይህ ቤይጂንግ ተጨማሪ እርምጃ እንድትወስድ ጫና ሊያሳድርባት ይችላል። ነገር ግን ቻይና ለረዥም ጊዜ ጣልቃ ያለመግባት ፖሊሲ ያላት ሲሆን እስካሁን ድረስ ለኢራን የረዥም ጊዜ ደህንነት ዋስትና ለመስጠት ፍላጎት አላሳየችም።

  10. ቻይና ለኢራን የጦር መሣሪያ ሸጣለች መባሉን አስተባበለች

    የቻይና ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ቻይና ለኢራን የጦር መሣሪያ አቅርባለች ወይንም ለማቅረብ ታስባለች የሚለው ውንጀላ መሠረተ ቢስ ነው ስትል አጣጣለች።

    ሰኞ ዕለት ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አገራቸው ለኢራን የጦር መሣሪያ አቅርባለች ወይም ለማቅረብ አቅዳ ነበር የሚለውን ዘገባ “መሠረተ ቢስ ውንጀላ” ሲሉ አጣጥለውታል።

    የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን የደህንነት ምንጮችን በመጥቀስ ቻይና ለኢራን የጦር መሣሪያ ታቀርባለች ሲሉ መዘገባቸውን ተከትሎ ስጋት ተፈጥሯል።

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቤይጂንግ ለቴህራን ወታደራዊ ድጋፍ አድርጋለች በሚል 50 በመቶ አዲስ ታሪፍ እንደሚጣልባት ዝተው ነበር።

    ቻይና የፕሬዚዳንቱን ውንጀላ ያስተባበለችው ሲኤንኤን ሦስት የአሜሪካ የደህንነት ምንጭ ጠቅሶ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ለኢራን አዲስ የአየር መቃወሚያ ስርዓት ልታቀርብ ነው ሲል መዘገቡን ተከትሎ ነው።

    በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ዘ ኒውዮርክ ታይምስ እንዲሁ የአሜሪካ ባለሥልጣናትን ጠቅሶ ቤጂንግ ትከሻ ላይ ተደርጎ የሚተኮስ ሚሳዔል ሳትልክ አትቀርም ብሏል።

    ቻይና እነዚህን ዘገባዎች በማስተባበል "ወታደራዊ ቁሳቁሶች ወደ ሌሎች አገራት በሚላክበት ወቅት የአገሪቱን የውጭ ንግድ ቁጥጥር ሕጎች እና ደንቦች እንዲሁም በዓለም አቀፍ ግዴታዎች መሠረት ጥብቅ ቁጥጥሮችን በመተግበር ሁልጊዜ ጥንቃቄ እና ኃላፊነት የተሞላበት እርምጃ እንወስዳለን” ብላለች።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጉኦ ጂያኩን “መሠረተ ቢስ ውንጀላዎችን ወይም ይሁነኝ ተብለው የሚደረጉ ማዛመዶችን እንቃወማለን” ሲሉ በዕለታዊ ጋዜጣዊ መግለጫቸው ወቅት ተናግረዋል።

  11. የእስራኤል መከላከያ ኃይል ሊባኖስ ላይ ጥቃት ሲፈፅም ሄዝቦላህ ደግሞ እስራል ላይ ሮኬት ተኮሰ

    የእስራኤል ጦር ተሽከርካሪ በደቡባዊ ሊባኖስ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    አሜሪካ የኢራንን ወደቦች እንደምትዘጋ ካሳወቀች በኋላም በመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነቱ ቀጥሏል።

    ዛሬ ሠኞ ሄዝቦላህ ድሮኖችን ተጠቅሞ ሸሎሜ በተባለ ስፍራ በሚገኙ የእስራኤል ወታደሮች ላይ ጥቃት መፈፀሙን አስታውቋል። እስራኤል በአካባቢው የአየር ጥቃት ማስጠንቀቂያ አውጥታለች።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ የእስራኤል መከላከያ ኃይል በደቡባዊ ሊባኖስ ዘመቻውን እያስፋፋ መሆኑን አስታውቋል።

    ቢንት ጅቢል በተባለ ስፍራ በፈፀመው ጥቃት 100 የሄዝቦላህ ተዋጊዎች መገደላቸውን እና በመቶዎች የሚቆጠር የጦር መሣሪያ በአካባቢው ማግኘቱን ገልጿል።

    እስራኤል እና ሊባኖስ በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ነገ ማክሰኞ ቀጥተኛ የሰላም ድርድር ለማድረግ ቀጠሮ ይዘዋል።

  12. የኢራን ጦር የአሜሪካ እርምጃ ‘የባሕር ላይ ውንብድና’ ነው አለ

    የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የኢራን ወታደራዊ ኃይል ዋሽንግተን የኢራን ወደቦችን ለመዝጋት ያሳለፈችው ውሳኔ ሕገ ወጥ እና የባሕር ላይ ውንብድና ነው አለ።

    ጦሩ የአጸፋ እርምጃ እንደሚወስድም ዝቷል።

    በአገሪቱ ብሔራዊ የዜና አገልግሎት በኩል በታተመ መግለጫ ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን መቆጣጠሯን ትቀጥላለች ያለ ሲሆን፤ ጦርነቱ ቢቋጭ እንኳ ከጠላት ጋር ግንኙነት ያላቸው መርከቦች በኢራን የውሃ ግዛት ላይ የመተላለፍ መብት የላቸውም ብሏል።

    የኢራን ጦር ሌሎች የባሕረ ሰላጤው አገራትን በማስጠንቀቅ፤ በቀጣናው የወደቦች ደኅንነት “ለሁሉም አልያም ለማንም አይሆንም” ብሏል።

    የኢራን ወደቦች በአሜሪካ ዒላማ ከሆኑ “በፋርስ ሰላጤ እና በኦማን ባሕር ማንም ደኅና አይሆንም” በማለት አስጠንቅቋል።

  13. የባሕር መስመርን መዝጋት ምን ማለት ነው? እንዴትስ ይሰራል?

    የአሜሪካ የጦር መርከብ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በአሜሪካ እአአ በ2022 የወጣው ሕግ የባሕር መስመርን መዝጋት “የሁሉም አገራት መርከቦች እና/ወይም አውሮፕላኖች፣ ጠላት እና ገለልተኛ ወገኖች፣ ወደተለዩ ወደቦች፣ አየር ማረፊያዎች፣ ወይም የባህር ዳርቻ አካባቢዎች በጠላት አገር ቁጥጥር ስር ያሉ ቦታዎች እንዳይገቡ ወይም እንዳይወጡ ለመከላከል የሚደረግ የጦር እንቅስቃሴ" በማለት ይበይነዋል።

    የአሜሪካ ባሕር ኃይል በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የሚያካሄዳቸውን ዘመቻዎች ይህንን ሕግ የተከተለ ይመስላል።

    የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንቲኮም) የኢራን ወደቦችን እንደሚዘጋ በመግለጽ ባወጣው መግለጫ ላይ “ከሁሉም በባሕረ ሰላጤው እና በኦማን ባህረ ሰላጤ ከሚገኙ የኢራን ወደቦች በሚነሱ በሁሉም አገራት መርከቦች ላይ ያለምንም ልዩነት ተግባራዊ የሚሆን” መሆኑን ጠቅሷል።

    ሴንቲኮም ከኢራን ወደቦች ውጭ የሚመጡ መርከቦች በወሽመጡ በኩል ማለፍ እንደሚችሉ እና ክልከላ እንደማይደረግባቸው አስታውቋል።

    የንግድ የባሕር ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎችም መስመሩ ከመዘጋቱ በፊት እንዲያውቁት እንደሚደረግ ተናግሯል።

    ፕሬዚዳንት ትራምፕ በወሽመጡ የሚገኙ የኢራን ወደቦችን በመዝጋት ሌሎች አገራትም እንደሚሳተፉ ገልጸዋል። ነገር ግን ይሳተፋሉ ያሏቸውን አገራት በስም አልጠቀሱም።

    ቢቢሲ ዩናይትድ ኪንግደም በዚህ ዘመቻ ላይ እንደማትሳተፍ ማወቅ ችሏል።

  14. አሜሪካ እዘጋቸዋለሁ ያለችው የኢራን ወደቦች እና ተጽዕኗቸው

    በቴህራን አደባባይ የተሰቀለ ግዙፍ ፖስተር

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    አሜሪካ እና ኢራን በፓኪስታን የሰላም ስምምነት ላይ መድረስ ባለመቻላቸው ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚገቡ እና የሚወጡ መርከቦችን እንደምታግድ አስታውቀዋል።

    የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም) የአሜሪካ ኃይል ባሕረ ሰላጤውን ጨምሮ ወደ ኢራን ወደቦች በሚገቡ እና በሚወጡ መርከቦች ላይ “ያለ ልዩነት” እገዳውን እንደሚያስፈፅም ገልጿል።

    ይሁን እንጂ ሴንትኮም የአሜሪካ ኃይሎች ከኢራን ወደቦች ውጭ በሚደረገው የመርከቦች ነፃ እንቅስቃሴ ላይ እንቅፋት እንደማይሆን አስታውቋል።

    በትሩዝ ሶሻል የማኅበራዊ ትስስር ገፅ ትራምፕ አሜሪካ ከሠኞ ጀምሮ በኢራን ወደቦች መርከቦች እንዳይንቀሳቀሱ እንደምትዘጋ ተናግረዋል።

    የመከላከያ ተንታኞች ይህ የአሜሪካ እርምጃ ኢራን ነዳጅ እንዳትሸጥ ያደርጋል ብለዋል።

    ጀስቲን ክራምፕ የተባሉ ተንታኝ የኢራንን ወደቦች ለመዝጋት ትራምፕ የያዙት እቅድ የኢራንን ጦርነት የበለጠ የሚያባብስ እና ስምምነት ባለመደረሱ “የትራምፕን ብስጭት የሚያንፀባርቅ” ነው ብለውታል።

    ዕቅዱ እንደ ቻይና ላሉ አገራት ኢራን ነዳጇን እንዳትሸጥ የሚያግድ ሲሆን፤ ይህም ኢራን ላይ ጫና ያሳድራል።

    አሜሪካ እና ኢራን አንዳቸው በሌላኛቸው ላይ የተሻለ የመደራደሪያ አቅም እንዳላቸው ያምናሉ ሲሉ የጠቆሙት ተንታኙ፤ ሁለቱም አገራት ማሸነፋቸውን ሌላውን ዝቅ በማድረግ ለማሳየት እየሞከሩ ነው ብለዋል።

    ይህም የበለጠ ውጥረት እና ውድመት እንደሚያስከትል ጠቁመው፤ በሳምንቱ መገባደጃ የተደረገው ድርድር ምንም እንኳ ፍሬ ባያፈራም “አዎንታዊ ተፅዕኖ” አሳድሯል የሚል ስሜት እንዳላቸውን ተናግረዋል።

    “ሰፊ ውይይት ማድረጋቸው መልካም ነው። የሚያወያይ ምንም ነገር ባይኖር ኖሮ ድርድሩ በፍጥነት ይጠናቀቅ ነበር” ብለዋል።

  15. የፕሬዝዳንት ትራምፕ ቀጣይ እርምጃ አሜሪካ ላይ የፈጠረው ስጋት

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Reu

    በምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ የተመራው የዲፕሎማት ቡድን ጦርነቱን ለማስቆም የሚያስችል ስምምነት ለማድረግ ሞክሮ ከከሸፈ በኋላ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሚቀጥለው እርምጃቸውን ወስነዋል።

    ይህን ውሳኔያቸውም እሁድ ዕለት ትሩዝ ሶሻል በተባለው ማኅበራዊ ትስስራቸው በተከታታይነት በለጠፏቸው ጽሑፎች ይፋ አድርገዋል።

    ትራምፕ አሜሪካ በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ ሚደረግ የመርከብ እንቅስቃሴ ታግዳለች ሲሉ ጽፈዋል።

    “ሕገ ወጥ ቀረጥ የከፈለ ሁሉ በባሕር ደኅንነት ያለው ጉዞ አያደርግም” ብለዋል።

    አሜሪካ ለአገራት የመርከብ ጉዞ ደኅንነት ለማረጋገጥ በሆርሙዝ ወሽመጥ ባሕር ውስጥ የተጠመዱ ፈንጂዎችን ማፅዳቷን ትቀጥላለችም ብለዋል።

    የአሜሪካ ጦር ለዚህ መዘጋጀቱን የጠቆሙት ትራምፕ “በተገቢው ወቅት” ኢራን ላይ ጥቃታቸውን ለመቀጠል ዝግጁ መሆናቸውንም ገልፀዋል።

    በፓኪስታን ኢስላማባድ ለ20 ሰዓታት የተደረገው ድርድር መሻሻል የታየበት መሆኑን ቢጠቅሱም ትራምፕ ኢራን የኒውክሌር ልማቷን እንድትገታ አሜሪካ ያስቀመጠችውን አቋም አታሟላም ብለዋል።

    የትራምፕ ልጥፎች ምንም እንኳ ባለፈው ሳምንት የኢራንን ሥልጣኔ ከምድረ ገፅ አጠፋለሁ እንደሚለው አውዳሚ ባይሆኑም እርምጃዎቹ በርካታ አዲስ ስጋቶችን ያዘሉ ናቸው። ለአሜሪካም ስጋት ነው።

    የባሕር ፈንጂዎችን ማፅዳት የአሜሪካ መርከቦች በኢራን እንዲጠቁ የበለጠ ተጋላጭ አያደርጋቸውም? አሜሪካ የኢራንን የመተላለፊያ ክፍያ ማን እንደሚከፍል በምን ልታውቅ ትችላለች? የመርከብ እግዱን የጣሱ የውጭ አገር ሰንደቅ ዓላምን በሚያውለበልቡ መርከቦች ላይ ኃይል ልትጠቀም ትችላለች? እንደ ቻይና ያሉ በኢራን ነዳጅ ላይ ጥገኛ የሆኑ አገሮች ምን ዓይነት ምላሽ ይሰጣሉ? የኢራንን ዋነኛ የገቢ ምንጭን ለማድረቅ የተወሰደው እርምጃ የነዳጅ ዋጋን ከዚህም በላይ ያንረዋል?

    ለእነዚህ መሠረታዊ ጥያቄዎች ግልፅ ምላሽ የለም።

  16. የዓለም የነዳጅ ዋጋ ዳግም ከ100 ዶላር በላይ ከፍ አለ

    የነዳጅ መቅጃ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የተደረገው ድርድር ያለ ስምምነት መጠናቀቁን ተከትሎ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኢራንን ወደቦች እንደሚዘጉ ከዛቱ በኋላ የነዳጅ ዋጋ በበርሜል ከ100 ዶላር በላይ አሻቀበ።

    የዓለም ነዳጅ ዋጋን የሚተምነው የብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት በ7.3 በመቶ ጭማሪ በማሳየት 102.30 ዶላር ተሸጧል።

    በሳምንቱ መጨረሻ ላይ የተደረገው ድርድር አለመሳካቱ የዓለም የኃይል ቀውስ እየተባባሰ ሊሄድ ይችላል የሚል ስጋትን አስነስቷል።

    ባለፈው ረቡዕ ዋሽንግተን እና ቴህራን የሆርሙዝ የባሕር ወሽመጥ የንግድ መተላለፊያን ለመክፈት የሁለት ሳምንት የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ከደረሱ በኋላ የነዳጅ ዋጋ ከ100 ዶላር በታች ወርዶ ነበር።

  17. የሆርሙዝ ወሽመጥ ለምን የዓለማችን ቁልፍ የባሕር መስመር ሆነ?

    የሆርሙዝ ወሽመጥ

    የሆርሙዝ ወሽመጥ በዓለም ላይ በጣም አስፈላጊው የስትራቴጂክ የኃይል መስመር ነው።

    የፋርስ ባሕረ ሰላጤን ከአረብ ባሕር ጋር ያገናኛል። በዓለም 39 በመቶ የሚሆነውን የባሕር ድፍድፍ ነዳጅ እና 19 በመቶው የተፈጥሮ ጋዝ ይተላለፍበታል።

    ከአብዛኛዎቹ ስትራቴጂካዊ መስመሮች በተለየ የባሕረ ሰላጤው አገራት ምርታቸውን የሚልኩበት ከሆርሙዝ ውጪ ሌላ አማራጭ የላቸውም።

    ኢራን ከ1980ዎቹ ጀምሮ የሆርሙዝ ወሽመጥን እንደምትዘጋ በየጊዜው ስታስፈራራ ቆይታለች።

    አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ግዛት ላይ የመጀመሪያውን የአየር ድብደባ ካከሄዱበት ቀን ጀምሮ የተከሰተው የመርከብ መስተጓጎል ግን በአስርት ዓመታት ውስጥ እጅግ የከፋው መሆኑ ተነግሯል።

    ይህ ክስተት በታሪክ ውስጥ ከፍተኛውን የነዳጅ አቅርቦት መስተጓጎል ከማስከተሉም በላይ በዓለም አቀፍ የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ ላይ አስደንጋጭ ጭማሪ ፈጥሮ ቆይቷል።

    በባሕረ ሰላጤው ውስጥ የተፈጠረው መስተጓጎል ከኢነርጂ ዘርፉ በላይ ተጽዕኖ አሳድሯል። የአካባቢው አገራት በየዓመቱ ከ26 ሚሊዮን በላይ ኮንቴይነሮችን ያስተናግዳሉ። ከፍተኛ መጠን ያለው ማዳበሪያም በዚሁ መንገድ ያልፋል።

    በወሽመጡ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ጉዞ መስተጓጎል ከተፈጠረ በዓለም አቀፍ የምግብ ምርቶች ላይ ቀጥተኛ ተጽዕኖ ይኖረዋል።

  18. ትራምፕ በኢራን ላይ ዳግም ጥቃት ለመክፈት እያጤኑ መሆኑን ዎል ስትሪት ጆርናል ዘገበ

    የአሜሪካ የጦር ጄት

    የፎቶው ባለመብት, Dalibor Ankovic / DA Photography

    አሜሪካ እና ኢራን በፓኪስታን ያካሄዱት ድርድር ሳይሳካ መቅረቱን ተከትሎ ትራምፕ ቴህራን ላይ ዳግም ጥቃት የመክፈት ሃሳብ እንዳላቸው ዎል ስትሪት ጆርናል ዘገበ።

    ዎል ስትሪት ጆርናል ስማቸውን ያልገለጻቸው የአሜሪካ ባለሥልጣናትን ጠቅሶ ከሌሎች እርምጃዎች በተጨማሪ ኢራን ላይ ድብደባ ለመጀመር እያጤኑ መሆኑን ዘግቧል፥።

    ትራምፕ እሁድ ዕለት የባሕር ኃይላቸው የሆርሙዝ ወሽመጥን እንዲዘጋ ትዕዛዝ ሰጥተዋል።

    ዋይት ሐውስ ቢቢሲ ስለ ጋዜጣው ዘገባ ላቀረበው ጥያቄ ሁሉም አማራጮች ጠረጴዛ ላይ ናቸው ሲል ምላሽ ሰጥቷል።

    የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ ኦሊቪያ ዌልስ “ፕሬዚዳንቱ የሆርሙዝ ወሽመጥን እንዲዘጋ ባሕር ኃይሉን አዝዘዋል። የኢራንን ዝርፊያ ያበቃል እና ሁሉንም ተጨማሪ አማራጮች በጠረጴዛው ላይ ተቀምጠዋል። ለዎል ስትሪት ጆርናል ፕሬዚዳንቱ ቀጥሎ የሚያደርጉትን መረጃውን የሰጠ ማንኛውም ሰው በግልጽ ግምቱን ነው ያስቀመጠው” ብለዋል።

  19. ትራምፕ ኢራን አሁንም የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ትፈልጋለች አሉ

    ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ኢራን እና አሜሪካ ያካሄዱት ድርድር ያለ ምንም ስምምነት ከተጠናቀቀ በኋላ ትራምፕ ቴህራን አሁንም የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ፍላጎት አላት ሲሉ ተናገሩ።

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ኢራን አሁንም የኒውክሌር ፍላጎት እንዳላት በኢዝላማባድ ድርድር ወቅት መናገሯን ጠቅሰዋል።

    “አሁንም ይፈልጋሉ፤ ይህንን ደግሞ የዚያን ዕለት ምሽት [ድርድር በተካሄደበት ዕለት] ግልጽ አድርገዋል። ኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ሊኖራት አይችለም።”

    ከዚህ በፊት ትራምፕ ከቴህራን ጋር ያደረጉት የቀጥታ ንግግር ያልተሳካውቴህራን “የኒውክሌር ፍላጎቶቿን ለመተው ፈቃደኛ ሳትሆን ስለቀረች ነው” ብለዋል።

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራጋቺ በበኩላቸው ሁለቱ አገራት ከስምምነት ለመድረስ “ስንዝር ቀርቷቸው ነበር” ካሉ በኋላ ነገር ግን አገራቸው “የተለጠጠ ፍላጎት፣ የግብ ለውጥ፣ የወደብ መዝጋት” እንደገጠማት ተናግረዋል።

  20. አሜሪካ የኢራን ወደቦቸን ከሰኞ ጀምሮ እንደምትዘጋ አስታወቀች

    በባሕር ላይ ቅኝት የሚያደርግ መርከብ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የአሜሪካ ጦር የኢራን ወደቦችን ከሰኞ ጀምሮ እንደሚዘጋ ገልጾ ነገር ግን በወሽመጡ ላይ ወደ ሌላ አገራት የሚንቀሳቀሱ መርከቦቸን ላይ “መስተጓጎል እንደማይፈጥር” አስታውቋል።

    ትራምፕ በበኩላቸው በዋሺንግተን አቅራቢያ በሚገኘው የአንድሪው የጦር ሠፈር ለጋዜጠኞች ኢራን ወደ ድርድሩ ባትመለስ “ምንም እንደማይሰማቸው” ተናግረዋል።

    “ተመለሱ አልተመለሱ ግድ አይሰጠኝም። ካልተመለሱም ችግር የለብኝም” ብለዋል።

    ትራምፕ ይህንን ያሉት በሁለቱ አገራት መካከል በፓኪስታን ኢዝላማባድ የተደረገው የቀጥታ ንግግር ሳይሳካ ከቀረ በኋላ ነው።

    ትራምፕ በሁለቱ አገራት መካከል የተደረሰው የተኩስ አቁም “በመልካም ሁኔታ እንደቀጠለ” መሆኑን ተናግረዋል።

    የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ወደ ኢራን ወደቦች የሚገቡ እና የሚወጡ መርከቦችን ሰኞ ዕለት ከ11 ሰዓት ጀምሮ (14:00 GMT) እንደሚዘጋ አስታውቋል።

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን “ሆን ብላ” የሆርሙዝ ወሽመጥን ዳግም ሳትከፍት ቀርታለች ካሉ በኋላ ወደቦቹ አንዲዘጉ አዝዘዋል።

    ፕሬዚዳንቱ የአሜሪካ ባሕር ኃይል ላይ ጥቃት ለመፈጸም የሚሞክር “መዓት እንደሚወርድበት” አስታውቀው ማንኛውም መርከብ በወሽመጡ ላይ ለማለፍ ቀረጥ እንዳይከፍል አስታውቀዋል።

    በአሜሪካ እና በኢራና መካከል በፖኪስታን የተደረገው ድርድር ሳይሳካ ቀርቶ ዳግም የተፈጠረውን ውጥረት ተከትሎ የነዳጅ ዘይት ዋጋ በበርሜል ከ100 ዶላር በላይ መሸጥ ጀምሯል።

    ትራፕም ከኢራን ጋር የተደረገው የቀጥታ ንግግር ያልተሳካለው “ኢራን የኒውክሌር ፍላጎቷን ለመተው ፈቃደኛ ሳትሆን ስለቀረች ነው” ሲሉ ወንጅለዋታል።

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራጋቺ በበኩላቸው ቴህራን “በቀና ልብ” በድርድሩ ላይ መሳተፏን ሲናገሩ የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባዔ ሞሐመድ ባጋር ጋልቢፍ ደግሞ ኢራን “ለማስፈራሪያዎች አትንበረከክም” ብለዋል።

    የኢራን አብዮታዊ ዘብ ወደ ወሽመጡ የሚጠጉ መርከቦች የተኩስ አቁሙን እንደጣሱ ይቆጠራሉ ሲል አስጠንቅቋል።

Trending Now