አሜሪካ በኢራን ጦርነት ያጣቻቸው የጦር አውሮፕላኖች

የፎቶው ባለመብት, Social media
እንደ አሜሪካ ባለሥልጣናት መግለጫ፣ የመገናኛ ብዙኃን ሽፋን እና የምሥል ትንተናዎች ከሆነ አሜሪካ እስካሁን ድረስ በጦርነቱ ቢያንስ ዘጠኝ አውሮፕላኖችን አጥታለች።
መጋቢት 27 2018 ዓ.ም.- ሲቢኤስ ኒውስ የአሜሪካ ባለሥልጣናትን ጠቅሶ እንደዘገበው “ኤፍ-15ኢ” ተዋጊ ጄትን ለማገዝ የተጓዙ ሁለት የትራንስፖርት አውሮፕላኖች ከኢራን መነሳት አልቻሉም። አውሮፕላኖቹ በጠላት እጅ እንዳይወድቁ በሚል እንዲወድሙ መደረጉ ተዘግቧል። የተረጋገጡ ምሥሎች አውሮፕላኖቹ በማዕከላዊ ኢራን እንደወደሙ አሳይተዋል። ቢቢሲ ቨሪፋይ የአውሮፕላኖቹን ዓይነት ለመለየት ባለሙያዎችን ጠይቋል።
መጋቢት 25- በማዕከላዊ ኢራን ተዋጊ ጄት ተመትቶ ወድቋል። ባለሙያዎች ከስብርባሪው ባገኙት መረጃ ተመትቶ የወደቀው ጄት “ኤፍ-15ኢ ስትራይክ ኤግል” የተባለው የአሜሪካ ተዋጊ ጄት መሆኑን ለቢቢሲ ቬሪፋይ ተናግረዋል። በተመሳሳይ ቀን ኒዮርክ ታይምስ የአሜሪካ ባለሥልጣናትን ጠቅሶ እንደዘገበው “ኤ-10” የተባለ ጄት በባሕረ ሰላጤው ተከስክሷል። አብራሪው ቀድሞ ተመንጥቆ በመውጣት ሊተርፍ ችሏል።
መጋቢት 20- ማረጋገጥ የቻልነው ምሥል “ኢ-13” የተባለ አውሮፕላን የኢራንን ጥቃት ተከትሎ በሳዑዲ አረቢያ ልዑል ሱልጣን አየር ጣቢያ ለሁለት መከፈሉን ያሳያል።
መጋቢት 3- “ኬሲ-135” የተባለ የነዳጅ መሙያ አውሮፕላን በምዕራብ ኢራቅ ተከስክሶ ስድስት ወታደሮች ሕይወታቸው ማለፉን የአሜሪካ ማዕከላዊ ኮማንድ (ሴንትኮም) አስታውቋል። ክስተቱ እየተመረመረ ቢሆንም ኮማንዱ በጠላት አሊያም በወዳጅ አገራት ተኩስ አለመውደቁን ግን ጠቁሟል።
የካቲት 23- ሦስት የአሜሪካ “ኤፍ-15ኢ” ጄቶች ሴንትኮም “በወዳጅ አገራት ያልተጠበቀ ክስተት” ሲል በገለፀው ሁነት በኩዌት ወድቀዋል። ስድስቱም አባላት አስቀድመው መውጣት መቻላቸውንም አክሏል። ቢቢሲ ቬሪፋይ ከተንቀሳቃሽ ምሥል ማረጋገጥ እንደቻለው ጄቶቹ በኩዌት ከተማ ምዕራባዊ ክፍል ወደ መሬት ሲሽከረከሩ ነበር።

















