ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከሆርሙዝ ወሽመጥ በተጨማሪ ለዓለም የባሕር ላይ እንቅስቃሴ ወሳኝ የሆኑት መተላለፊያዎች የትኞቹ ናቸው?
በኢራን ላይ የተካሄደው ጦርነት የኢነርጂ እና የሸቀጦችን ገበያ አውኳል። አገሪቱ ለነዳጅ ጭነት ወሳኝ የሆነውን የሆርሙዝ ወሽመጥን ዘግታ ቆይታለች። ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ ለማለፍ የሞከሩ ከአስራ ሁለት በላይ መርከቦች ላይ ጥቃት ፈጽማለች።
ዶናልድ ትራምፕ በአውሮፓ የሚገኙ የአሜሪካ አጋሮች የባሕር ወሽመጡን እንዲጠብቁ ጫና ለማሳደር ሞክረዋል። አሜሪካ የሆርሙዝ ወሽመጥን እንደገና ለመክፈት የምታደርገውን ጥረት ካልደገፉ "የኔቶ የወደፊት ዕጣ ፈንታ በጣም መጥፎ" እንደሚሆን አስጠንቅቀው ነበረው።
በባሕረ ሰላጤው የተፈጠረው የመርከብ ጉዞ መስተጓጎል የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ ከፍ እንዲል አስገድዷል። ቀውሱ ከመጀመሩ በፊት አንድ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ከነበረበት ከ70 የአሜሪካ ዶላር አሁን ከ100 የአሜሪካ ዶላር በላይ እንዲደርስ አደርጎ ነበር።
ከሸቀጣ ሸቀጦች እስከ ግብርና ግብዓቶች ያሉ ዓለም አቀፍ ንግዶችም ተጽዕኖው አርፎባቸዋል።
ቀውሱ የዓለም ንግድ አነስተኛ መጠን ባላቸው ጠባብ መተላለፊያዎ ላይ የተመሠረተ መሆኑን አሳይቷል።
ቀጥለን ለዓለም አቀፍ ንግድ በጣም አስፈላጊ የሆኑ ወሽመጦችን እና ተጋላጭነታቸውን እንመለከታለን።
1. የሆርሙዝ ወሽመጥ
የሆርሙዝ ወሽመጥ በዓለም ላይ በጣም አስፈላጊው የስትራቴጂክ የኃይል መስመር ነው። የፋርስ ባሕረ ሰላጤን ከአረብ ባሕር ጋር ያገናኛል። በዓለም 39 በመቶ የሚሆነውን የባሕር ድፍድፍ ነዳጅ እና 19 በመቶው የተፈጥሮ ጋዝ ይተላለፍበታል።
ከአብዛኛዎቹ ስትራቴጂካዊ መስመሮች በተለየ የባሕረ ሰላጤው አገራት ምርታቸውን የሚልኩበት ከሆርሙዝ ውጪ ሌላ አማራጭ የላቸውም።
ኢራን ከ1980ዎቹ ጀምሮ የሆርሙዝ ወሽመጥን እንደምትዘጋ በየጊዜው ስታስፈራራ ቆይታለች።
አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ግዛት ላይ የመጀመሪያውን የአየር ድብደባ ካከሄዱበት ቀን ጀምሮ የተከሰተው የመርከብ መስተጓጎል ግን በአስርት ዓመታት ውስጥ እጅግ የከፋው መሆኑ ተነግሯል።
ይህ ክስተት በታሪክ ውስጥ ከፍተኛውን የነዳጅ አቅርቦት መስተጓጎል ከማስከተሉም በላይ በዓለም አቀፍ የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ ላይ አስደንጋጭ ጭማሪ ፈጥሮ ቆይቷል።
በባሕረ ሰላጤው ውስጥ የተፈጠረው መስተጓጎል ከኢነርጂ ዘርፉ በላይ ተጽዕኖ አሳድሯል። የአካባቢው አገራት በየዓመቱ ከ26 ሚሊዮን በላይ ኮንቴይነሮችን ያስተናግዳሉ። ከፍተኛ መጠን ያለው የማዳበሪያም በዚሁ መንገድ ያልፋል።
በወሽመጡ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ጉዞ መስተጓጎል ከተፈጠረ በዓለም አቀፍ የምግብ ምርቶች ላይ ቀጥተኛ ተጽዕኖ ይኖረዋል።
2. የሱዊዝ ካናል
ሱዊዝ ካናል ቀይ ባሕርን ከሜዲትራኒያን ጋር ያገናኛል። በእስያ እና በአውሮፓ መካከል የሚደረገውን ጉዞ ቢያንስ በአስር ቀናት ይቀንሳል።
ይህ የባሕር መተላለፊያ 10 በመቶ የሚሆነውን የዓለም የባሕር ላይ ንግድ ያስተናግዳል። 22 በመቶ የሚሆነውን የኮንቴይነር ጉዞ፣ 20 በመቶ የመኪና ጭነት እና 10 በመቶ የድፍድፍ ነዳጅ በሱዊዝ ካናል ይተላለፋል።
መተላለፊያው በግብፅ ቁጥጥር ስር በመሆኑ በቀላሉ አደጋ ላይ አይወድቅም። መንገዱ ከአደጋዎች የራቀ ግን አይደለም። ኤቨር ጊቨን የተሰኘው የኮንቴይነር መርከብ በ2021 መስመሩን መዝጋቱ የሚዘነጋ አይደለም።
መርከቡ ሱዊዝ ካናልን ለስድስት ቀናት በመዝጋቱ ወደ 10 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚጠጋ የንግድ ልውውጥ ተስተጓጉሏል።
የዚህ ስትራቴጂካዊ መንገድ ትልቁ ተጋላጭነት ያለው በቀይ ባሕር ደቡባዊ ጫፍ ላይ በሚገኘው የባብ ኤል-መንደብ ወሽመጥ ላይ ነው።
እስራኤል በጋዛ ከሐማስ ጋር ላደረገችው ጦርነት ምላሽ ለመስጠት በሚል ከ2023 እስከ 2025 ድረስ በኢራን የሚደገፈው ሁቲ በንግድ መርከቦች ላይ የሰነዘረው ጥቃት ብዙ የመርከብ ድርጅቶች አቅጣጫቸውን እዲቀይሩ አስገድዷቸዋል።
ይህ ሁኔታም በሱዊዝ ካናል የሚደረገውን ጉዞ በ2023 ከነበረበት 26 ሺህ በላይ መርከቦች በ2024 ወደ 13 ሲህ ገደማ እንዲወርድ አስገድዷል።
የሁቲ መሪዎች በቅርቡ አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ የፈጸሙት ጥቃት ለመበቀል በንግድ መርከቦች ላይ የሚሰነዘሩትን ጥቃት እንደገና እንደሚጀምሩ አስጠንቅቀዋል።
3. የፓናማ ቦይ
የፓስፊክ እና የአትላንቲክ ውቅያኖሶችን የሚያገናኘው የፓናማ ቦይ 2.5 በመቶ የሚሆነውን የዓለም የባሕር ንግድን ያስተናግዳል። ድርሻው አነስተኛ ቢሆንም ስትራቴጂካዊ እና ከፍተኛ ዋጋ ባላቸው ጭነቶች የሚተላለፉበት ነው።
ቦዩ ከዩናይትድ ስቴትስ ምርት ውስጥ 40 በመቶውን ሚያስተናግድ ሲሆን፣ ይህም በየዓመቱ 270 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚያወጣ ዋጋ ያለው ነው።
ቦዩ ለአየር ንብረት እና ለጂኦፖለቲካ ውጥረት ተጋላጭ ነው። በ2023 እና 2024 በነበረ ከባድ ድርቅ ምክንያት ቦዩ የውሃ ማጠራቀሚያዎች ውስጥ ያለው የውሃ መጠን በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀንስ አድርጓል። ይህም በመርከቦች ብዛት እና መጠን ላይ ገደብ እንዲጣል አስገድዷል።
በ2025 መጀመሪያ ላይ ደግሞ ትራምፕ ቦዩን መቆጣጠር እንደሚፈልጉ ተናግረው ነበር። የሆንግ ኮንግ ኩባንያ ወደቦቹን የሚያስተዳድርበት መንገድ ላይ ያላቸውን ስጋት ጠቅሰዋል።
4. የማላካ ወሽመጥ
የማላካ ወሽመጥ በዓለም ላይ በጣም ሥራ የሚበዛበት የመርከብ መስመር ነው። 24 በመቶውን የዓለም የባሕር ንግድን ያስተናግዳል። 45 በመቶ ድፍድፍ ነዳጅ እና 26 በመቶ የሚሆኑ መኪኖችን በዚሁ ወሽመጥ በኩል ያልፋሉ።
በዓለም ላይ ሁለተኛው ግዙፍ የኮንቴይነር ወደብ ባለቤት የሆነችው ሲንጋፖርም በዚሁ የውሃ መስመር ላይም ትገኛለች።
ማላካ ቻይና፣ ጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ የኃይል ፍላጎታቸውን የሚያገኙበት ዋነኛው መተላለፊያ ነው። ወደ 80 በመቶ የሚጠጉ የቻይና ነዳጅ በዚህ መስመርበኩል ያልፋል። ቤይጂንግ "የማላካ አጣብቂኝ" ስትል ያላትን ጥገኝነት ትገልጻለች።
የባሕር ላይ ዝርፊያ ዋነኛው ስጋት ነው። በ2025 በማላካ ወሽመጥ ከ130 በላይ ክስተቶች ሪፖርት ተደርገዋል። ትልቁ አደጋ ግን ጂኦፖለቲካዊ ነው።
በቻይና እና በአሜሪካ ወይም በሕንድ መካከል በአካባቢው የባሕር ኃይል የበላይነት ላይ የሚፈጠር ማንኛውም ውጥረት መስመሩን በእጅጉ ሊያስተጓጉል ይችላል።
ማላካ እንደ ሱናሚ እና እሳተ ገሞራ ላሉ የተፈጥሮ አደጋዎች ተጋላጭ ነው። ለምሳሌ በአውሮፓውያኑ 2004 የተከሰተው ሱናሚ ወደ በደቡባዊ መግቢያው ላይ የሚገኙ መሠረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አስከትሏል።
5. የቱርክ የባሕር ወሽመጥ
የቱርክ የባሕር ወሽመጥ በጥቁር ባሕር እና በሜዲትራኒያን መካከል ያለው ብቸኛው የባሕር መተላለፊያ ነው።
ሦስት በመቶ የሚሆነው የዓለም የባሕር ንግድ በዚህ በኩል ይተላለፋል። ቁጥሩ አነስተኛ ሊመስል ቢችልም፤ ከዩክሬን፣ ከሩሲያ እና ከሮማኒያ የሚላከው 20 በመቶው የዓለም የስንዴ ምርት መተላለፊያ ነው።
በኢስታንቡል፣ ቱርክ በኩል በጣም ጠባብ የሆነው ቦታው 700 ሜትር ስፋት አለው። በዚህ ምክንያትም ለመተላለፍ አስቸጋሪ እና ጥቃቅን ግጭቶች በተደጋጋሚ የሚከሰቱበት ነው።
በሞንትሩክስ ስምምነት መሠረት ቱርክ የባሕሩ ወታደራዊ እንቅስቃሴን ትቆጣጠራለች። በ2022 ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች በኋላ በአካባቢው የጦር መርከቦችን እንቅስቃሴ ለመገደብ መተላለፊያውን ስትጠቀምበት የቆይታለች።
በጥቁር ባሕር ክልል ውስጥ ተጨማሪ ግጭት ከተፈጠረ ይህንን ሚዛን ሊያዛባ እና የዓለም የእህል ገበያን ሊያስተጓጉል ይችላል። በአካባቢው የሚከሰተው ከፍተኛ የመሬት መንቀጥቀጥ ተጨማሪ ስጋት ይፈጥራል።
በሆርሙዝ ወሽመጥ የተፈጠረው ቀውስ የዓለም ንግድ ለተለያዩ ግጭቶች እና ተፈጥሯዊ አደጋዎች በከፍተኛ ደረጃ ተጋላጭ መሆኑን አጉልቶ አሳይቷል። የዓለም የንግድ መስመሮች እነነዚህ ከላይ የተጠቀሱት አምስት መስመሮች ብቻ ግን አይደሉም።
በዓለም ላይ እስከ 24 የሚደርሱ ስትራቴጂካዊ የባሕር መስመሮች አሉ። እንደ ታይዋን፣ ዶቨር እና ቤሪንግ ያሉ የባሕር ወሽመጦችም አስፈላጊ የውሃ መስመሮችን ናቸው።