ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሌተናንት ጄነራል ታደሰ የሥልጣን ዘመን መራዘም "ሕጋዊ" መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ለቢቢሲ ገለጸ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፤ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ታደሰ ወረደን የሥልጣን ዘመን ያራዘሙት ከፕሪቶሪያ ስምምነት በኋላ በወጣው ሕግ መሠረት በመሆኑ "ሕጋዊነት" እንዳለው ጽሕፈት ቤታቸው ለቢቢሲ ገለጸ።
ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት)፤ የፌደራል መንግሥትን ውሳኔ ተቃውሞ ባወጣው መግለጫ የሌተናንት ጄነራል ታደሰ ሥልጣን የተራዘመው "ከፕሪቶሪያ ስምምነት በፊት በወጡ ሕጎች" እንደሆነ ጠቅሶ ነበር።
የፕሬዝዳንቱ ሥልጣን መራዘሙ ይፋ በተደረገበት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የረቡዕ ዕለት መግለጫ ላይ የተጠቀሰውም በ2013 ዓ.ም. በትግራይ ጦርነት ወቅት የወጣ እና ከፕሪቶሪያ ስምምነት በኋላ የተሻረ ደንብ ነበር።
በጦርነቱ ወቅት የተቋቋመውን እና በዶ/ር ሙሉ ነጋ ሲመራ የነበረውን የመጀመሪያውን የክልሉን ጊዜያዊ አስተዳደር የመሠረተው ይህ ደንብ ከፕሪቶሪያ ስምምነት በኋላ ተሽሯል። ከፕሪቶሪያ ስምምነት በኋላ ክልሉን የመሩት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ የተሾሙት በ2015 ዓ.ም. በወጣ አዲስ ደንብ ነው።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም ዛሬ አርብ ሚያዝያ 2/2018 ዓ.ም. ለቢቢሲ በጽሑፍ መልዕክት በሰጡት ምላሽ በመግለጫው ላይ የተሻረው ደንብ የተጠቀሰው "በስህተት" እንደሆነ ገልጸዋል።
ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊዋ "በእኛ በኩል የተፈጠረ የአጠቃቀስ ስህተት ነው፤ ይስተካከላል" ብለዋል። ይህ ዘገባ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ መግለጫው ላይ ማስተካከያ አለመደረጉን ቢቢሲ ተገንዝቧል።
ቢልለኔ፤ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት ሥልጣን በአንድ ዓመት የተራዘመው በ2015 በወጣው እና ባለፈው ዓመት በተሹመበት ደንብ መሠረት እንደሆነ በምላሻቸው አብራርተዋል።
የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊዋ፤ የሥልጣን ዘመን "ማራዘሚያው የተደረገው ከአንድ ዓመት በፊት ሹመት ሲሰጥ መሠረት በነበረው በዚህ [የ2015] ደንብ መሠረት ነው" ብለዋል። በዚህም መሠረት ሥልጣን የማራዘም ውሳኔው "ሕጋዊ ነው" በማለትም ገልጸዋል።
ይህንን የፌደራል መንግሥት ውሳኔ በተመለከተ ትናንት ሐሙስ ሚያዝያ 1/2018 ዓ.ም. ምሽት መግለጫ ያወጣው ህወሓት፤ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ሌተናንት ጄነራል ታደሰ ወረደ ሥልጣንን በአንድ ዓመት እንዲራዘም መደረጉ "የተናጠል ውሳኔ" እንደሆነ በመግለጽ ተቃውሟል።
በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የሚመሠረተው "በሁለቱ ተፈራራሚ አካላት ማለትም በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ እና በኢትዮጵያ መንግሥት" መካከል በሚደረግ "ፖለቲካዊ ንግግር" እንደሆነ በመግለጫው ጠቅሷል።
"ብዙ መደናቀፎች እያጋጠሙ ቢቆዩም"፤ ከፕሪቶሪያ ስምምነት መፈረም በኋላ በ2015 ዓ.ም. የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የተቋቋመው በሁለቱ አካላት መካከል "በተደረጉ ንግግሮች" እንደሆነ አስታውሷል።
"ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ መንግሥት እየፈፀማቸው የቆዩት የፕሪቶሪያው ስምምነት የመጣስ ተግባራት [ቀጥሏል]" ሲል በዚህ ሳምንት ስለተራዘመው የፕሬዝዳንት ታደሰ የሥልጣን ቆይታ አንስቷል።
እንደ ህወሓት ገለጻ የፌደራል መንግሥት የጊዜያዊ አስተዳደሩን ቆይታ በአንድ ዓመት ያራዘመው "ከፕሪቶሪያ ስምምነት በፊት የነበሩ ሕጎችን መሠረት" በማድረግ እንዲሁም የዘላቂ ተኩስ አቁም ስምምነቱን "ሙሉ በሙሉ በመጣስ" ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ የሌተናንት ጄነራል ታደሰን ሥልጣን ማራዘማቸው ይፋ በተደረገበት የጽሕፈት ቤታቸው መግለጫ ላይ የተጠቀሰው፤ የትግራይ ጦርነት ከተጀመረ በኋላ በ2013 ዓ.ም. የወጣው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ነው።
ከጦርነቱ መጀመር በኋላ የተመሠረተው እና በዶ/ር ሙሉ ነጋ ሲመራ የነበረውን የመጀመሪያ ጊዜያዊ አስተዳደር ለማቋቋም የወጣው ደንብ ከፕሪቶሪያ ስምምነት በኋላ ተሽሯል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊዋ ለቢቢሲ በሰጡት ምላሽ ቢልለኔ የአጠቃቀስ ስህተት እንደሆነ የጠቀሱት ይህንን ደንብ ነው።
ይህንን ደንብ የተካው በሥራ ላይ ያለ ደንብ፤ የጊዜያዊ አስተዳደሩን ፕሬዝዳንት የመሾም ሥልጣንን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጠ ቢሆንም ርዕሰ መስተዳደሩ የሚለየው "በሰላም ስምምነቱ መሠረት በሚደረግ የፖለቲካ ምክክር" እንደሆነ ደንግጓል።
ህወሓት ትናንት ባወጣው መግለጫ የጊዜያዊ አስተዳደሩን የሥልጣን ቆይታ የማራዘም ውሳኔውን "የሁለቱ ተፈራራሚ አካላት ንግግር ያልተደረገበት" እና "የተናጠል ውሳኔ" ሲል ገልጾታል።
"ከህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ እውቅና እና ተሳትፎ ውጪ የተላለፈ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የተናጠል ውሳኔ መሆኑ ለመላው ሕዝባችን፣ የፕሪቶሪያው ስምምነት አደራዳሪ አካላት እና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንዲገነዘቡት እንወዳለን" ብሏል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊዋ በህወሓት ስለቀረበው ፖለቲካዊ ንግግር አልተደረገም የሚል ክስ እስካሁን ምላሽ አልሰጡም።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ረቡዕ ዕለት ባወጣው መግለጫ የፕሬዝዳንቱ የሥልጣን ዘመን በአንድ ዓመት እንዲራዘም የተወሰነው በቀረበው ሪፖርት፣ የፌደራል መንግሥት በክልሎች ውስጥ ጣልቃ የሚገባበትን ሥርዓት ለመደንገግ በወጣው አዋጅ እና "የትግራይ ክልል አካታች ጊዜያዊ አስተዳደር አስመልክቶ በጸደቀው ደንብ" እንደሆነ አስታውቋል።