እስራኤል እና ሊባኖስ ከሦስት አስርት ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ፊት ለፊት ተገናኝተው ተወያዩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሊባኖስ እና እስራኤል ከሦስት አስርት ዓመታት በኋላ የመጀመሪያውን የዲፕሎማሲ ውይይት በዋሺንግተን አደረጉ።
ይህ ውይይት በእስራኤል እና በኢራን በሚደገፈው ሄዝቦላህ መካከል የተቀሰቀሰውን ግጭት ለማስቆም መንገድ ይጠርጋል ተብሎ ተገምቷል።
በሁለቱ አገራት መካከል አደራዳሪ ሆነው የተገኙት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ የሄዝቦላህን ተጽዕኖ ለማስቆም "ታሪካዊ ዕድል" እንደሆነ ተናግረዋል።
አሜሪካ ያወጣችው መግለጫ ሁለቱ ወገኖች ወደፊት በሚገለጽ ጊዜ እና ቦታ በቀጥታ ድርድር ለመጀመር መስማማታቸውን ይገልጻል።
እስራኤል ሁሉንም መንግሥታዊ ያልሆኑ የሽብር ቡድኖችን ትጥቅ ማስፈታት እንደምትፈልግ ተናግራለች። ይህም የሄዝቦላህ ታጣቂዎችን ለማመልክት የተጠቀመችበት ነው።
ሊባኖስ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ እና የሰብአዊ ቀውሷን ለመፍታት እርምጃዎችን እንድትወስድ ጥሪ አቅርባለች። ሁለቱ አገራት የዲፕሎማሲ ግንኙነት የሌላቸው ሲሆን በመካከላቸው የመጨረሻው ቀጥተኛ እና በከፍተኛ ባለሥልጣናት ደረጃ ውይይት ያደረጉት እአአ በ1993 ነበር።
አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ጦርነት በጀመሩ በጥቂት ቀናት ውስጥ ሄዝቦላህ ወደ እስራኤል ሮኬቶችን እና ድሮኖችን ማስወንጨፉን ተከትሎ የእስራኤል ጦር በሊባኖስ ወታደራዊ ዘመቻ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከ2,000 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።
ሁለቱ ወገኖች ማክሰኞ ዕለት በዋሽንግተን ሲገናኙ ሄዝቦላህ በሊባኖስ በሚገኙ የእስራኤል ወታደሮች እና በእስራኤል ላይ ቢያንስ 24 ጥቃቶችን እንደፈፀመ ተነግሯል።
በሰሜናዊ እስራኤል ድሮን እና ሮኬቶች መተኮሳቸውን ተከትሎ የአደጋ ጊዜ ደወሎች ተሰምተዋል።
እስራኤል በሊባኖስ የምታደርገው ወታደራዊ ዘመቻ በጋዛ ጦርነት ወቅት እአአ በ2023 እና 2024 የተዋጋችውን ሄዝቦላህን ትጥቅ ለማስፈታት እና ለማፍረስ ያለመ መሆኑን ተናግራለች።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ቶሚ ፒጎት ከውይይቱ በኋላ በሰጡት መግለጫ እስራኤል እና ሊባኖስ የሄዝቦላህን ተጽዕኖ ለመቀነስ ለመስራት መስማማታቸውን ተናግረዋል።
ሊባኖስ በበኩሏ በአገሪቱ ውስጥ ያለውን ከባድ የሰብአዊ ቀውስ ለመፍታት እና ለማቃለል "ተኩስ እንዲቆም እና ተጨባጭ እርምጃዎች" እንዲወሰዱ ጥሪ ማቅረቧን ተናግረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ አሜሪካ "እስራኤል ከሄዝቦላህ ጥቃቶች ራሷን የመከላከል መብቷን እንደምትደግፍ" ገልጻለች።
ሩቢዮ ከስብሰባው በፊት ለጋዜጠኞች ውይይቱ "ሂደት" መሆኑን ተናግረዋል።
"ይህ ጊዜ ይወስዳል፣ ነገር ግን ይህ ጥረት ዋጋ እንዳለው እናምናለን" ብለዋል። "በዚህ ላይ ለመገንባት የምንፈልገው ታሪካዊ ስብሰባ ነው።"
የሊባኖስ ፕሬዝዳንት ጆሴፍ አውን በሰጡት መግለጫ ውይይቱ "በአጠቃላይ የሊባኖስ ሕዝብ እና በተለይም በደቡብ አካባቢ በሚኖሩ ዜጎች ላይ የሚደርሰው ስቃይ የሚያበቃበት ጊዜ መጀመርያ እንደሚሆን" ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል።
ለግጭቱ "ብቸኛው መፍትሔ" የሊባኖስ የጦር ኃይሎች "ለአካባቢው ደህንነት ብቸኛ ተጠያቂ መሆን" እንደሆነ ተናግረዋል።
የሊባኖስ መንግሥት ሄዝቦላህን ለመጋፈጥ ያለው አቅም ግን ውስን ነው።
ከውይይቱ በፊት የድርጅቱ ከፍተኛ አባል ለኤፒ የዜና ወኪል እንደተናገሩት በዋሽንግተን የሚስማሙበትን ማንኛውንም ጉዳይ እንደማያከብር ተናግረዋል።
"እኛ በሚስማሙበት ጉዳይ ተገዢ አንሆንም" ሲሉ የሄዝቦላህ የፖለቲካ ምክር ቤት አባል የሆኑት ዋፊቅ ሳፋ ተናግረዋል።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1982 የተመሰረተው ሄዝቦላህ በሚገባ የታጠቀ ቡድን ሲሆን በሊባኖስ የሺዓ ሙስሊሞች በብዛት በሚኖሩበት የአገሪቱ ደቡባዊ ክፍል እንዲሁም በዋና ከተማዋ ቤይሩት ደቡባዊ ዳርቻዎች በስፋት ይንቀሳቀሳል።
አሜሪካ እና ኢራን በፓኪስታን ባደረጉት ውይይት የኢራን ተደራዳሪዎች ሊባኖስ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ውስጥ እንድትካተት አጥብቀው ጠይቀዋል። ነገር ግን አሜሪካም ሆነ እስራኤል በዚህ እንደማይስማሙ ተናግረዋል።
አንድ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለሥልጣን ለቢቢሲ እንደተናገሩት የእስራኤል እና የሊባኖስ ውይይት የታቀደው ከአንድ ወር በፊት ነው።
በእስራኤል ዘመቻ ከተገደሉት ከ2,000 በላይ ሊባኖሳውያን በተጨማሪ፣ በግጭቱ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል።















